አባይ ሚዲያ ሃምሌ፤2012

ግብጽ የኢትዮጵያ መንግሥት በአስቸኳይ ስለ ግድቡ ውሃ ሙሌት ማብራሪያ እንዲሰጣት መጠየቋ ተሰምቷል ግብጽ ማወቅ የምትፈልገው ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ኢትዮጵያ ሆን ብላ መሙላት መጀመር አለመጀመሯን ማወቅ እንደሆነ ተጠቅሷል ኢትዮጵያ ሱዳንና ግብጽ እያደረጉት የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር መቋረጡ እንደተሰማ ነበር የግድቡ ውሃ መጠን እየጨመረ መሆኑን የሚያሳዩ የሳተላይት ምስሎች መውጣት የጀመሩት።

ሱዳን በበኩሏ በታችኛው አገራት ያለው የውሃው ፍሰት በቀን 90 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትሮች መቀነሱን ገልፃለች ኢትዮጵያ ግድቡን በይፋ መሙላት አለመጀመሯን ተናግራለች 5 ቢሊየን ዶላር የይፈጃል የተባለው ይህ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን መካከል ድርድር እየተደረገበት ቆይቷል።

በታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውሃ ሙሌት መጀመሩን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ማስታወቁን የአገር ውስጥ ሚዲያዎች የዘገቡ ቢሆንም በይፋ አለመጀመሩን ሚኒስትሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ የግድቡ ሙሌት መጀመሩን አስመልክቶ በሰጡት ምላሽ ዘገባው “በስህተት የወጣ ነው፤ የራስ ትርጉም ተጨምሮበታል።

ግድቡ ግንባታው አሁን የደረሰበት ደርሷል፤ ግድቡ ውሃ ይይዛል እንጂ በይፋ የተጀመረ ነገር የለም” ብለዋል ከዚህ በተጨማሪ ሚኒስትሩ ለአሶሺየትድ ፕሬስ እንደተናገሩት እነዚህ የሳተላይት ምስሎች የሚያሳዩት ከፍተኛ ዝናብ መኖሩንና ከግድቡ ከሚወጣው ይልቅ ግድቡ ውስጥ የሚገባው መጨመሩን ነው ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ዶ/ር ስለሺ እንደገለጹት ባለፈው ዓመት ውሃው ያልፍ የነበረው በ520 ከፍታ ላይ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት 560 ከፍታ ላይ መድረሱን ተናግረዋል ከ560 ከፍታ በታች ያለው ውሃ ግድቡ ውስጥ የሚቀር እንደሆነና ሙሌቱም ከግንባታው ሂደት ጋር የማይነጣጠል ነው ማለታቸውንም የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በተያያዘ መረጃ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገው ድርድር ቀጣይነት እንደሚኖረው  ሚኒስትሩ ገልጸዋል ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በሰጡት መግለጫ በግድቡ ዙሪያ በሚደረግ ድርድር የታችኛው ተፋሰስ አገራት ከህግ ማዕቀፍ አንጻር አሳሪ አንቀጽ ለማስገባት የሚያደርጉት ጥረት ለ11 ቀናት ሲካሄድ የነበረው ድርድር ያለ ስምምነት እንዲጠናቀቅ ቢያደርግም ቀጣይነት እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

“በድርድሩ ይዘን የምንቀርበው ሀሳብ የዛሬውም ቀጣዩም ትውልድ ውሃ መጠቀም የሚያስችለው መብት ተገቢ ባልሆነ አንቀፅ እንዳይታሰር የሚያደርግ ነው” ብለዋል ድርድሩ ጥንቃቄ እና ብስለት በተሞላበት መንገድ እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል ይህ እየተደረገ ያለው ኢትዮጵያ እየለማች እና እየበለፀገች በምትሄድበት ወቅት የግድቡ አጠቃቀም ላይ የማሻሻያ ህጎች በማስፈለጋቸው ነው ብለዋል።

በግድቡ አሞላል፣ በግድቡ ደህንነት እና መረጃ ልውውጥ ግልፅ እንደሆነና በአንዳንድ የህግ ማዕቀፎች ላይ ስምምነት እንዳልተደረሰ ተናግረዋል የግድቡ ግንባታ  በተጠና መልኩ የሚካሄድ ስለሆን የውሃ ሙሌት እና የግድቡ ግንባታ አብሮ የሚከናወን ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል የግድቡ ውሃ ሙሌት  የማንንም ፈቃደኝነት እንደማይጠይቅና የድርድሩ አካል አለመሆኑንም አብራርተዋል።