አባይ ሚዲያ ሃምሌ፤2012

የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ በሚመለከት በኦሮሞ ፖለቲካ ሃይሎች ዘንድ የተለያዩ ገለጻዎች መደረጋቸውን ሲቀጥሉ በተለይም ሀጫሉን የገደለው ኦነግ ሸኔ ነው፤ እና ሀጫሉን የገደለው ነፍጠኛ የተባለው የጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ መንግስት ነው፤ የሚሉት ወገኖች ጽንፍ በያዘ ጎራ ሆነው መሟገታቸው የአደባባይ ምስጢር ሆኗል፡፡

የሀጫሉን ገዳይ የጠ/ሚ ዐቢይ መንግስት የሚያደርገው ክስ፤ ነፍጠኛ በሚለው ስያሜ በተጠሩ የአመጽ ቅስቀሳዎች በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የንጹሃን ግድያንና የንብረት ውድመትን በማስተናገዱ ከፍተኛ ጥፋት ደርሷል በተለይም በድምጻዊው ግድያ ሰሞን በውጭ ሀገራት በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ በጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ መንግስት ላይ በቀረበው ወቀሳና ውንጀላ ዶ/ር ዐቢይ ሳይቀሩ ነፍጠኛ ናቸውና መሰል ተቃውሞዎች መቅረባቸው የቅርብ ቀን ትዝታ ነው፡፡

ትላንት በኦቢኤን ቴሌቪዥን በተላለፈው የጠ/ሚ ዐቢይ ቃለ መጠይቅ ላይ ለሀገሪቱ መሪ ኦሮሞ አይደሉምና የኦሮሞን ህዝብ ክደዋል ተብሎ ለሚነሳባቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ተደምጠዋል ጠ/ሚ ዐቢይ ኦሮሞ አይደለም ተብሎ የሚወራውና ጥያቄ የሚነሳው አሁን ነው ያሉ ሲሆን ቤተመንግስት ከመግባቴ በፊትና የኦሮሞን ትግል ስመራ እንዲሁም በትግሉ ስሳተፍ እንዲህ አይባልም ነበር ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ያም አለ ይህ ኦሮሞነቴን ያሳደገኝ ማህበረሰብም ሆነ ለኦሮሞ ትግል የከፈልነውን ዋጋ የሚያውቅ ይሄን ጥያቄ አያነሳም ያሉት ዶ/ር ዐቢይ ምንም እንኳ ኦሮሞነት በደም ብቻ ሳይሆን በተግባርም የሚገለጽ ቢሆን አባቴና እናቴ ኦሮሞ መሆናቸውም ሆነ በሻሻ ተወልጄ ማደጌ ብቻውን ኦሮሞነቴን ይገልጻል የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የኦሮሞን ህዝብ ክደዋል እየተባለ ነው የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ጠ/ሚ ዐቢይ ሲመልሱ ኦሮሞን መካድ ራስንና ቤተሰብን መካድ ነው፤ ይሄን ጥያቄ እያነሱ መነጋጋሪያ የሚያደርጉት ከዚህ በፊት ከሀገራቸው የሸሹና ከቤተሰባቸው ርቀው የነበረው አሁን ግን በእኔ ጥረት ከቤተሰባቸው ጋር መሆን የቻሉ ናቸው ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ በሁለት ነገር ይታወቃል፤ በአንድ በኩል ጭቆናን ያስተናገደና በአምባገነኖች መከራን ያየ ሲሆን በሌላ በኩል ሀገር በመገንባትና የገዳ ስርዓትን በማጎልበት የሚታወቅ ነው ያሉት ጠ/ሚ ዐቢይ ነገር ግን እኔ እያለሁ ከዚህ በኋላ ኦሮሞ አይጨቆንም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ዐቢይ እኔ ያለሁት ከአቃፊው፤ ወላጅ አልባውን ከሚያሳድገውና የተበተነውን ከሚሰበስበው ኦሮሞ ጋር ነኝ ፤ ምክናየቱም ትክክለኛው የኦሮሞ ባህሪ ይሄ ነው ያሉ ሲሆን የኦሮሞነት አቃፊነት የሚተውና ከሌሎች ጋር መኖርን የማይፈልጉ ሃይሎች የሚሉት ኦሮሞነት አይደለም ሲሉ ገልጸዋል እነዚህ የኦሮሞን ባህሪ የማይገልጽ ተግባር ላይ ያሉ አካላት ዘግይተውም ቢሆን የእኛ ሀሳብ ይገባቸዋል ያሉት ጠ/ሚ ዐቢይ ኦሮሞ እንደሰፊነቱ አንድነቱን በማጠናከር ከሌሎች ኢትዮጵያን ጋር በአሮነትና ሀገር በመገንባት ሂደቱ መቀጠል እንዳለበት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡